(አዲስ አበባ 22/1/2016 ዓ.ም) ስልጠናውን በውይይት ያስጀመሩት የኤች አይቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ባለሙያ ገንዘብ ደሳለኝ እንዳሉት ከዚህ በፊት በመንግስት ፣ በተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች በተደረገ ርብርብ የኤች አይ ቪ ስርጭት ቀንሶ እንደነበር አስታውሰው መዘናጋቱ በዚሁ ከቀጠለ ካለፈው ጊዜ በባሰ ሁኔታ ሀገራችንን ዋጋ ያስከፍላል ብለዋል :: የኤች አይ ቪ ስርጭት ምጣኔ በ 2023 ዜሮ ለማድረስ ቢታቀድም በታቀደው ልክ መስራት እንዳልተቻለ ያብራሩት ባለሙያዋ በማስተዋልና የኤች አይ ቪ ጉዳይን በሥራችን እያካተትን በመስራት ሰራተኞችን በማወያየት ስርጭቱን ለመቀነስ ጥረት መደረግ አለበት ብለዋል ::
ስልጠናው የኤች አይ ቪ ኤድስ ቁልፍ እውነታዎች በሚል ርዕስ ከጤና ጥበቃ ሚንስትር በመጡ አቶ መኮንን የተሰጠ ሲሆን የኤች አይ ቪ አሁናዊ መረጃ በዓለምና በኢትዮጵያ እንዲሁም ከተማችን በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ውይይት ተደርጓል:: አቶ መኮንን በስልጠናው ወቅት ኤች አይ ቪ ከገጠር ይልቅ በከተማ ያለው ስርጭት ሰፊ መሆኑን አውስተው እንደ አዲስ አበባ አሁንም የኤች አይ ቪ ስርጭት አሳሳቢ መሆኑን በመረዳት ቅንጅታዊ አሰራርን በማስፈን ሁሉም በእኔነት ስሜት እንዲሰራ ማድረግና የድጋፍና ክብካቤ ስራን ማጠናከር እንዲሁም ሜንስትሪሚንግ ላይ ጠንክሮ በመስራት ሥርጭቱን መግታት አለብን ብለዋል :: አያይዘውም ቢሮዎች ሁሉንም ሰራተኞች በኤድስ ፈንድ ላይ በማሳተፍና የኤች አይ ቪ ሴክተር ሜንስትሪሚንግን በማበረታታት አምራች የሆነውን የሰው ኃይልን በመጠበቅ ኤች አይ ቪን መቆጣጠር መቻል አለባቸው ብለዋል ::
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወ /ሮ ታጋይቱ አባቡ በስልጠናው መዝጊያ ላይ በመገኝት ባስተላለፉት መልዕክት ሰራተኛው በስልጠናው የተላለፈውን መልእክት ችላ ሳይል የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት እንዳይስፋፋ ራሱንና ቤተሰቡን መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል ::
የቢሮው አዳዲስ ሰራተኞችም የኤድስ ፈንድን በመቀላቀል ድጋፍ ለሚፈልጉ ህፃናትና በኤች አይ ቪ የተጎዱ ወገኖችን እንዲያግዙ ጥሪ ቀርቧል ድጋፍም ተሰጥቷል::
0 Comments