አዲስ አበባ ነሀሴ 29/2015 ዓ.ም በውይይቱ የቢሮው አጠቃላይ ሰራተኞች የተሳተፉ ሲሆን በመርሀ ግብሩ ከመሪ እቅዱ ባሻገር የቢሮው የመልካም አስተዳደር እቅድና ከተለያዩ ተቋማት ጋር በትስስር የተከናወኑ ተግባራት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የቢሮ ኃላፊ አማካሪ ወይዘሮ አበበች ነጋሽ በውይይቱ መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት የ2016 ዓ.ም መሪ እቅድ ቀደም ብሎ በቢሮው የማኔጅመንት አባላትና ጄነራል ካውንስል አባላት ተገምግሞ ከመጽደቁ ባሻገር በቅርቡ በተካሄደው 30ኛው ከተማ አቀፍ የትምህርት ጉባኤ ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበት ገልጸው እቅዱ በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆንም ሆነ የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ እንዲችል የቢሮው ባለሙያዎች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ባለሙያዎቹ በእቅዱ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ በመያዝ ወደተግባር መግባት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
በመርሀ ግብሩ የቢሮው የ2016ዓ.ም መሪ እቅድ በእቅድና በጀት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጌታሁን ለማ የቀረበ ሲሆን መሪ እቅዱ በ11 ዋና ዋና ግቦች ስር የተቀመጡ የተለያዩ አላማዎችን ለማሳካት መታቀዱን አቶ ጌታሁን ጠቁመው እቅዱን በአግባቡ ተግባራዊ ለማድረግ 2.1 ቢሊየን ብር በካፒታል እና መደበኛ በጀት መያዙንም ገልጸዋል።
የቢሮው የለውጥና መልካም አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ከበደ በበኩላቸው በ2016ዓ.ም ከቢሮ እስከ ትምህርት ቤት ድረስ የተለዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እና የቢሮውን የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ፣የሌብነትና ብልሹ አሰራር መታገያ እቅድ አቅርበው በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጓል።
በመድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ጳግሜን ለኢትዮጵያ በሚል መሪ ቃል የ2015 ዓ. ም ጳግሜ ቀናት በተለያየ መርሃ ግብር ለማክበር ዝግጅት እያደረገ መሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ሲሳይ እንዳለ ገልጸው በነዚህ ጳግሜ ቀናት የሚካሄዱ መርሃ ግብሮች ቀኑን ከማክበር ባለፈ የቢሮ አገልግሎት ደረጃችንን ካለፉት አመታት በተሻለ ደረጃ በማሻሻል ስራችንን በአግባቡ የምንፈፅምበት እንዲሆን ያግዛል ብለዋል ::
ባለፉት አመታት በከተማ ደረጃ የጳግሜን ቀናት የተለያዩ ስያሜዎች በመስጠት ሲከበር መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን በዚህ ዓመትም የአገልግሎት ቀን ፣ የመስዋእትነት ቀን ፣ የበጎነት ቀን ፣ የአምራችነት ቀን ፣ የትውልድ ቀን እና የአብሮነት ቀን በሚል ስድስቱን የጳግሜ ቀናት በተለያዩ መርሃ ግብሮች ይከበራሉ::
0 Comments