ቀን 10/10/2014 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የ7ኛው ከተማ አቀፍ የሳይንስ ፈጠራ አውደ ርዕይ አካል የሆነ የጥናትና ምርምር የውይይት መድረክ አካሄደ።
በጥናትና ምርምር መድረኩ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሳነ መምህራንና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው የትምህርት አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳታፊ የሆኑ ሲሆን በውይይቱ የሳይንስ ትምህርት ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ያለው ፋይዳ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጥናት እንዲሁም በአዲስ አበባ በተመረጡ ትምህርት ቤቶች በ2014 ዓ.ም አንደኛ መንፈቅ አመት የ4ኛ ክፍል የፈተና አወጣጥን የተመለከተ ጥናት ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል።
በመርሀ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ እንዳስታወቁት በትምህርት ዙሪያ የሚደረግ የጥናትና ምርምር ስራ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው በዛሬው መርሀ ግብር ለውይይት በቀረቡ ጥናቶች የታዩ ግኝቶችን መሰረት በማድረግ የተለያዩ ስራዎችን በመስራት የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋይዛ መሀመድ በበኩላቸው የትምህርት ሴክተሩ ተመራማሪና ችግር ፈቺ ትውልድ የሚቀረጽበት ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰው የከተማው ምክር ቤት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚከናወኑ የተለያዩ ተግባራት የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
0 Comments