የመሰረታዊ ጎልማሶች ትምህርት መጽሐፍ ትውውቅ ተደረገ ::

by | ዜና

(ጥቅምት 22/2017 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የልዩ ፍላጎት አካቶ ትምህርትና ጎልማሶች መሰረታዊ ትምህርት ትግበራ ዳይሬክቶሬት በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ማዕቀፍ መሰረት በአማርኛና አፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች የተዘጋጀ የጎልማሶች መማሪያና አመቻች መምሪያ መጽሃፍት ትውውቅ አድርጓል፡፡

በአማርኛና አፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች የተዘጋጁት የጎልማሶች መማሪያና አመቻች መምሪያ መጽሃፍት ጎልማሶች የማንበብ ፣ መፃፍና ፣ ማስላት መሰረታዊ ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ በቋንቋ ፤ ሳይንስና ሂሳብ ትምህርቶች ላይ ትኩረት በማድረግ የተዘጋጀ እንደሆነና ቀደም ሲል በጎልማሶች ትምህርት የተሳተፉም ሆነ ያልተሳተፉ ከ15 ዓመት በላይ የሆኑ ወጣቶችና ጎልማሶች በስልጠናው መሳተፍ እንደሚችሉ ተገልጿል::

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ እና የዘርፉ ሀላፊ ወ/ሮ ታጋይቱ አባቡ በመፅሐፍ ትውውቁ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት ዘመናዊ ከተማን በመፍጠር ሥራ ውስጥ የተለወጠ ዜጋ ማፍራት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው ፤ ቢሮው ይህን የተለወጠ ዜጋ ለመቅረጽ እያደረገ ካለው ጥረት አንዱ የጎልማሶች ትምህርት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የጎልማሶች ትምህርት በተለያየ ሁኔታ በመደበኛ ትምህርታቸውን መከታተል ላልቻሉ ሴቶች ወጣቶችና ጎልማሶች መሰረታዊ ክህሎቶችን እንደሚያስጨብጥ የተናገሩት ምከትል ቢሮ ሃላፊዋ ትምህርቱ ለጎልማሶች መሰረታዊ እውቀት ከማስጨበጥ ባለፈ የሕይወት ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ ይረዳል ብለዋል፡፡

አያይዘውም ቢሮው የጎልማሶችን መፅሐፍ በሁለቱም ቋንቋዎች በማዘጋጀት መሰረታዊ የሆነ የስሌት ፤ ሳይንስና ቋንቋ ትምህርቶች እውቀት እንዲኖራቸው ለማድረግ በሚደረገው ጥረት በመፅሐፍ ትውውቁ የተሳተፉ አመቻች ባለሙያዎች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረው ፤ ጎልማሶችም ቢሮው ባመቻቸው መሰረታዊ የጎልማሶች ትምህርት በመጠቀም ራሳቸውን እንዲለውጡ ጠይቀዋል::

የልዩ ፍላጎትና አካቶ ትምህርትና ጎልማሶች መሰረታዊ ትምህርት ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ትእግስት ድንቁ ቀደም ሲል የጎልማሶች መማሪያ መፀሐፍ ብቻ ሲዘጋጅ እንደነበር አስታውሰው ፤ በሁለቱም ቋንቋዎች ከመማሪያ መጽሃፍ በተጨማሪ የአመቻች መፅሐፍ መዘጋጀቱ አመቻቹ የመፅሐፉን ይዘት በመረዳት በአግባቡ ተደራሽ እንዲያደርግና የማስተማሪያ ስልቶችን በማወቅ የተቀመጡ ጭብጦችን በአግባቡ ለማስተላለፍ የሚጠቅም መሆኑን አብራርተዋል :: ዳይሬክተሯ አክለውም መፀሐፉ ጎልማሶች ለሚኖራቸው የሕይወት ክህሎት ያለው ፋይዳ ትልቅ መሆኑን ገልፀው የመፅሐፍ ዝግጅቱ የተጠናቀቀ በመሆኑ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ አመቻቾች ተቀራራቢ ግንዛቤ ኖሯቸው እንዲያስተምሩ የማስተዋወቅ ስራ መሰራቱ ጠቃሚ መሆኑን አብራርተዋል ::

በመጽሓፍ ማስተዋወቅ ስነስርዓቱ ላይ አጠቃላይ የስርአተ ትምህርት ማዕቀፍ ሰነድ የጎልማሶችና መደበኛ ያልሆነ ትምህርት ባለሙያ በሆኑት አቶ ጌታቸው በላይ የቀረበ ሲሆን ፤ በአማርኛና አፋን ኦሮሞ ስርዓተ ትምህርቶች የተዘጋጁ የመማሪያና አመቻቾች መምሪያ መፅሐፍ ጭብጥና ይዘቶች በወ/ሮ ፍሬሕይወት አሰፋ እና በአቶ ረቢራ ዱጋሳ አማካኝነት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በመፅሐፍ ትውውቁ ከሁሉም ክፍለ ከተሞቸ የተውጣጡ አስተባባሪዎች ፣ ቡድን መሪዎች ፣ የጎልማሶችና መደበኛ ያልሆነ ትምህርት ባለሙያዎችና አመቻቾች ተሳትፈዋል::

0 Comments