የመምህራን ትምህርት አመራር ልማት ዳይሬክቶሬት ሞጁል የማላመድ (Module Adaptation) ሥራ መጀመሩን አሳወቀ::

by | ዜና

(ጥቅምት 29/2017 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የመምህራን ትምህርት አመራር ልማት ዳይሬክቶሬት ትምህርት ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያዘጋጀውን ሞጁል የአዲስ አበባን ነባራዊ ሁኔታ ባማከለ መልኩ የማላመድ ሥራ እያካሄደ እንደሆነ አሳውቋል ::

ሞጁሉ ለቅድመ አንደኛ ፣ አንደኛ ደረጃና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውጤታማ የትምህርት ቤት አመራር ለመፍጠር እና የትምህርት ቤት መሻሻልን እንዴት መምራት ይቻላል በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረት በማድረግ የሚዘጋጅ መሆኑን ያብራሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የመምህራን ትምህርት አመራር ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ተስፋዬ አድማሱ ከሞጁል ዝግጅት በኃላ በተዘጋጀው ሰነድ ላይ የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጥቶ ስልጠናውን እስከታች የማውረድ ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል::

የሚዘጋጁት ሞጁሎች ብቃትና ክህሎት ያለው የትምህርት አመራር በማፍራትና የትምህርት ቤት መሻሻል በመፍጠር የተማሪዎችን ውጤትና ስነምግባር ለማሻሻል ቢሮው እየሰራ ላለው ሥራ አቅም የሚፈጥር መሆኑ ተገልፃል::

የሞጁል ዝግጅቱ በዩኒሴፍ (UNICEF) ድጋፍ የሚካሄድ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ መምህራን ትምህርት አመራር ባለሙያዎች ፣ የስርዓተ ትምህርት ባለሙያዎች ፣ የፈተና ክፍል ባለሙያዎችና ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ የመምህራን ልማት ቡድን መሪዎች በትብብር የሚዘጋጅ መሆኑን ከዳይሬክቶሬቱ ያገኘነው መረጃ ያሳያል::

0 Comments