ወላጆች በ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ለሚያስመዘግቡዋቸው ተማሪዎች የልደት ሰርተፊኬት ማውጣት እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ከአዲስ አበባ የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ጋር በጋራ በመሆን በትምህርት ቤቶች በሚመዘገቡ ኩነቶች ዙሪያ በከተማና ክፍለከተማ ከሚገኙ የተቃማቱ አመራሮች ጋር ውይይት አካሄደ፡፡

በትምህርት ቤቶች የሚካሄድ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ የትምህርት ስርአቱን ዘመናዊ ከማድረግ ባሻገር በመረጃ የተደገፈ የትምህርት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ተግባር መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ገልጸው ኤጀንሲው በ2016 ዓ.ም የሚመዘገቡ አዳዲስ ተማሪዎችም ሆኑ ነባር ተማሪዎች የልደት ሰርተፊኬት እንዲኖራቸው ለማድረግ የያዘው እቅድ ስኬታማ እንዲሆን በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት አመራሮች አስፈላጊውን የንቅናቄ ስራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ በበኩላቸው ኤጀንሲው በአዲስ አበባ ዘመናዊ የወሳኝ ኩነት ስርአት በመፍጠር ለሌሎች ክልሎች ሞዴል ለመሆን የያዘው እቅድ ተግባራዊ እንዲሆን በትምህርት ቤቶች የሚካሄድ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው ምዝገባው በትምህርት ቤቶች ታብሌቶችን በመጠቀም እንደሚካሄድና ለዚህም ከወዲሁ የንቅናቄ ስራ ለመስራት ቅድመዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

ዳይሬክተሩ አክለውም አሁን በወጣው መርሀግብር መሰረት ለተማሪዎች የሚሰጠው የልደት ሰርተፊኬት  ለመጨረሻ ጊዜ በመሆኑ በመንግስትም ሆነ በግል ትምህርት ቤት የሚማሩ እና የልደት ሰርተፊኬት ያላወጡ ተማሪ ወላጆች አጋጣሚውን አጋጣሚውን ተጠቅመው ለልጆቻቸው ሰርተፊኬቱን ከየትምህርት ቤቱ ማውጣት እንደሚገባቸው አስረድተዋል፡፡

0 Comments

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SITE VISITORS

  • 0
  • 178
  • 249
  • 2,414
  • 8,966
  • 243,948
  • 243,948