ተደራሽ አካታችና ፍትሀዊ የትምህርት አገልግሎት ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች! በሚል በሚል መሪ ሀሳብ ለድጋፍ መስጫ ማዕከላትና ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ድጋፍ ተደረገ፡፡

by | ዜና

(አዲስ አበባ 22/1/2016 ዓ.ም)  ድጋፉ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች እና ለነሱ ድጋፍ እንዲሰጡ የተቋቋሙ የድጋፍ መስጫ ማዕከላትን በቁሳቁስ ለማደራጀት ታስቦ የተደረገ ሲሆን ቁሳቁሶቹን ከየክፍለከተማው የተውጣጡ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ተረክበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በመርሀ-ግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት ከተማ አስተዳደሩ የትምህርት ፍትሀዊነትን እና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልጸው የልዩ ፍላጎት ትምህርት  የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ እንዲችል ከቢሮ ጀምሮ እስከ ትምህርትቤት ድረስ በባለቤትነት የሚመራ አደረጃጀት ተዋቅሮ ተማሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙም አስረድተዋል፡፡

ኃላፊው አክለውም የዛሬው ድጋፍ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ተማሪዎች እንደየፍላጎታቸው የመማሪያ ቁሳቁስ አግኝተው በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑን በመጥቀስ ተማሪዎቹም የተደረገላቸውን ድጋፍ ተጠቅመው በትምህርታቸው ውጤታማ መሆን እንደሚገባቸው ጠቁመው  ቢሮው ለተማሪዎቹ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ወንድሙ ኡመር በበኩላቸው የዛሬው ድጋፍ በከተማ አስተዳደሩ ለሚማሩ ለሁሉም የልዩ ፍላጎት  ተማሪዎችና በ2015 ዓ.ም ለተደራጁ 18 የድጋፍ መስጫ ማዕከላት የሚደረግ መሆኑን ጠቅሰው በ2016 ዓ.ም የሚደራጁ 14 አዳዲስ የልዩ ፍላጎት ትምህርት የድጋፍ መስጫ ማዕከላትም በቀጣይ ተመሳሳይ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ገልጸዋል፡፡

ለተማሪዎቹ ከተደረጉ ድጋፎች መካከል ብሬል፤የብሬል ወረቀት፤መቅረጸ ድምጽ፤ኬን፤ቴሌቪዝን እንዲሁም መቀመጫዎችን ጨምሮ የተለያዩ የመማሪያ ቁሳቁሶች ይገኙበታል፡፡

0 Comments

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SITE VISITORS

  • 0
  • 187
  • 249
  • 2,423
  • 8,975
  • 243,957
  • 243,957