በውይይቱ በበጀት አመቱ ከቢሮ እስከ ትምህርት ቤት ድረስ የተከናወኑ ተግባራት ሪፖርት በቢሮው የእቅድና በጀት ዝግጅትና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሆኑት በአቶ ጌታሁን ለማ ከመቅረቡ ባሻገር በትምህርት ቤቶች ያለውን የመማር ማስተማር ስራ በተመለከተ የተካሄደ የሱፐርቪዥን ሪፖርት በአጠቃላይ ትምህርት ሱፐርቪዥን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጸጋዬ አሰፋ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል።


የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በውይይቱ ባስተላለፉት መልዕክት በ2015 ዓ.ም ዘጠኝ ወራት በከተማ አስተዳደሩ በትምህርት ዘርፉ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸው የዛሬው ውይይት እስካሁን የተከናወኑ ተግባራትን በመገምገም የታዩ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን መሰረት በማድረግ በቀጣይ ውጤታማ ስራ ለመስራት ከባለድርሻ አካላት መወያየት አስፈላጊ በመሆኑ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
ዶክተር ዘላለም አክለውም በተመረጡ ትምህርት ተቋማት የተደረገው ሱፐርቪዥን ትምህርት ቤቶች የተማሪዎችን ውጤትና ስነ-ምግባር ለማሻሻል ያከናወኗቸው ተግባራት ምንያህል ውጤታማ እንደሆኑ ለማወቅ ታስቦ መካሄዱን ጠቁመው ቢሮው በቀጣይ ቀናት በሁሉም ትምህርት ቤቶች ከአመራር ብቃት ጀምሮ ያለውን አጠቃላይ የመማር ማስተማር ሂደት የተመለከተ ምልከታ እንደሚያደርግም አስገንዝበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አሊ ከማል በበኩላቸው ውይይቱ ባለፉት 9ወራት ቢሮው ያከናወናቸውን ተግባራት በመገምገም በቀሪ የትግበራ ወቅት የተሻለ ስራ መስራት እንዲቻል እና በትምህርት ቤቶች በተካሄደው የሱፐርቪዥን ግብረ መልስ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት የጋራ ግንዛቤ ላይ ለመድረስ እንደሚረዳ አስረድተዋል።

በውይይቱ የሁሉም ክፍለከተማና ወረዳ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎችን ጨምሮ ርዕሳነ መምህራን እና በየደረጃው የሚገኙ ሱፐርቫይዘሮች የተሳተፉ ሲሆን ተሳታፊዎች በቀረቡ ሪፖርቶች ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችን እና አስተያየቶችን አቅርበው በቢሮ ኃላፊዎች ምላሽ ተሰጥቶ ውይይቱ ተጠናቋል።
