በ2014 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱ 896 ሺህ 520 ተማሪዎች መካከል ከ50 በመቶ በላይ ያመጡ ተማሪዎች ቁጥር 29 ሺህ 909 ተማሪዎች መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የ2014 ትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ላይ ሪፖርትና ዋና ዋና ግኝቶች በትምህርት ሚኒስቴር መግለጫ ተሰጥቷል።

የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ የፈተና አሰጣጡ ከዚህ ቀደም ከነበሩት የተለየ እንደነበርና በሁሉም የሚመለከታቸው አካል ርብርብ በስኬት የተጠናቀቀ እንደነበር አንስተዋል።

በፈተና ወቅትም ምንም አይነት ስርቆት ሳይደረግ የተጠናቀቀ ሲሆን አሁን የተለቀቀው ውጤትም በፈተና ወቅት ሲኮርጁ የነበሩ ተማሪዎችን በማውጣት በስርዓቱ የተፈኑ ተማሪዎችን ብቻ ያካተተ መሆኑን አስታውቀዋል።

በአጠቃላይ ለፈተናው 985 ሺህ 384 ተማሪዎች የተመዘገቡ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የተፈተኑና ውጤታቸው የተያዘላቸው ተማሪዎች ቁጥር 896 ሺህ 520 መሆኑን አስረድተዋል።

ከዚህ ውስጥ በፈተናው ተመዝግበው ያልተገኙ 77 ሺህ 98 ተማሪዎች ሲሆኑ 20 ሺህ 170ዎቹ ደግሞ በፈተናው ተገኝተው በተለያዩ የደንብ ጥሰቶች እንዳይፈተኑ የተደረጉና ፈተናውን ትተው የሄዱ ተማሪዎች ናቸው ብለዋል።

በአጠቃላይ በወጣው የፈተና ውጤትም በሀገር አቀፍ ደረጃ የተገኘው አማካይ ውጤት 29 ነጥብ 5 በመቶ ነው።

በመግለጫውም፥ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተመዘገበው ከፍተኛ ውጤት ከሰባት መቶ 666 በተፈጥሮ ሳይንስ ሲሆን፤ ከማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ ከስድስት መቶ 524 መመዝገቡ ተጠቅሷል።

በተፈጥሮ ሳይንስ 600 እና ከዛ በላይ ያስመዘገቡ 263 ተማሪዎች መኖራቸውም በመግለጫው ላይ ተመልክቷል።

በማህበራዊ ሳይንስ በአጠቃላይ 500 እና ከዛ በላይ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ 10 ተማሪዎች መሆናቸውም ተጠቅሷል።

ፈተናውን ከወሰዱ ተማሪዎች ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ ያመጡ ተማሪዎች ብዛት 29 ሺህ 909 ሲሆን ይህም ከአጠቃላይ ተፈታኞች 3 ነጥብ 3 በመቶ ነው ተብሏል።

በክልሎች ደረጃ በዉጤት ደረጃ  አዲስ አበባ፣ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም የሃረሪ ክልል የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በሃገር አቀፍ ደረጃ ፈተናውን ካስፈተኑ ትምህርት ቤቶች ውስጥ  ሰባት ትምህርት ቤቶች ያስፈተኑትን ተማሪዎች 100% አሳልፈዋል ተብሏል፡፡

ወደ ዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት ያላመጡ ተማሪዎች በማጠናከሪያ (remedial)  ፕሮግራም እንደ ዩኒቨርስቲዎቹ የመቀበል አቅም ተማሪዎችን ውጤት መሰረት አድርጎ በሚጸም የምልመላ መስፈርት ለዚህ ዓመት ብቻ ወደ ዩኒቨርስቲዎች  ገብተው በልዩ ሁኔታ በደከሙባቸው የትምህርት ዓይነቶች የተሻለ ዉጤት እንዲያስመዘግቡ የሚያስችል ድጋፍ ተደርጎላቸዉ ፈተና ተፈትነው የሚያልፉ ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርታቸውን እንድቀጥሉ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ ይህ የፈተና ውጤት ለዓመታት ሲንከባለል የቆየ የበርካታ ችግሮች መገለጫ እና ተሸፍኖ የቆየውን እውነተኛ የትምህርት ስርዓተ ያለበትን ደረጃ ያመላከተ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ለዚህም ተጠያቂው ከመንግስት ጀምሮ ሁሉም የትምህርት ማህበረሰቡ መሆኑንም ነው የገለጹት።

ይህን ውጤት ለመቀየር አጠቃላይ ሀገር አቀፍ የትምህር ስርዓቱን ለመቀየር አዲስ ስትራቴጂን ለማዘጋጀት መታቀዱን አስታውቀዋል። ከ50 በመቶ በታች ያመጡ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ እንደማይቀላቀሉ የተገለጸ ሲሆን ነገር ግን የዩኒቨርሲቲዎችን የመቀበል አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት በውጤታቸው መሰረት ተጨማሪ ተማሪዎችን በመቀበል ለቀጣይ ዓመት ዩኒቨርሲቲ መግባት የሚያስችላቸውን ውጤት እንዲያገኙ ይሰራል መባሉን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዘግባል።

0 Comments

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SITE VISITORS

  • 0
  • 0
  • 175
  • 2,114
  • 9,135
  • 234,185
  • 234,185