በግል ትምህርት ቤቶች በተካሄደ የ2015 ዓ.ም የኢንስፔክሽን ግኝትና በ2016 ዓ.ም ትምህርት አጀማመር ዙሪያ ከተቋማቱ ባለቤቶች ጋር ውይይት ተካሄደ።

by | ዜና

(ጥቅምት 27/2016 ዓ.ም)   ውይይቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ከአዲስ አበባ የትምህርት ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር በመተባበር ያካሄዱ ሲሆን በመርሀ – ግብሩ በትምህርት ቤቶቹ የተደረገ ሱፐርቪዥንና ኢንስፔክሽን ግኝት ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጓል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በመርሀ-ግብሩ እንደገለጹት የግል ትምህርት ተቋማት በትምህርት ልማት ስራው ለመንግስት አጋዥ በመሆን የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው ተቋማቱ መንግስት ያዘጋጀውን እና ዘንድሮ በሁሉም የትምህርት እርከኖች ተግባራዊ የሆነውን ስርዓተ ትምህርት በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባቸው በመግለጽ ቢሮው ለተቋማቱ አቅም በፈቀደ መጠን የሚጠበቅበትን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን አስታውቀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዳኛው ገብሩ በበኩላቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የግል ትምህርት ተቋማት ለትምህርት ስርዓቱ ውጤታማነት እያበረከቱ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ ለተቋማቱ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው የግል ትምህርት ቤቶችም ፍቃድ የወሰዱት የሀገሪቱን ስርዓተ ትምህርት ተግባራዊ ለማድረግ እንደመሆኑ ህግና ስርዓትን አክብረው መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው በመጥቀስ ባለስልጣኑም በተቋማቱ በሚያደርገው ክትትል ከስርዓተ ትምህርት ጥሰትም ሆነ ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተገናኘ የሚስተዋሉ ችግሮች ካሉ በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ህጋዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በመርሀ ግብሩ ማጠቃለያ በ2015 ዓ.ም በተካሄደ ኢንስፔክሽን ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ የግል ትምህርት ቤቶች ዕውቅና ተሰቷል።

 

0 Comments

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SITE VISITORS

  • 0
  • 205
  • 158
  • 7,078
  • 31,331
  • 147,475
  • 147,475