በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ 179 የፈተና ጣቢያዎች የ2014 ዓ.ም የ8ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና በዛሬው እለት ተጀመረ፡፡

by | ዜና

ቀን 27/10/2014 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ 179 የፈተና ጣቢያዎች የ2014 ዓ.ም የ8ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና በዛሬው እለት ተጀመረ፡፡

ፈተናው ከሚሰጥባቸው ጣቢያዎች መካከል ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሚገኘው አጼ ቴውድሮስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንዱ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ፤የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዘመኑ ደሳለኝ፤የከንቲባዋ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ አቶ ጥላሁን ፍቃዱን ጨምሮ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደፍርስ ኮራ እና የትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊዋ ሙሉ በላቸው በጣቢያው ተገኝተው የፈተና ሂደቱን ተመልክተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ የፈተና አጀማመሩን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት በ2014 ዓ.ም በከተማ አስተዳደሩ በ179 የመፈተኛ ጣቢያዎች 71,832 ተማሪዎች ፈተናውን እንደሚወስዱ ገልጸው በዛሬው እለት ፈተናው በሁሉም መፈተኛ ጣቢያዎች ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መልኩ መጀመሩን በመጥቀስ ምልከታ ባደረጉበት የፈተና ጣቢያ ተማሪዎች በስነ ልቦና ዝግጁ ሆነው ፈተናቸውን በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ ማረጋገጣቸውን አስረድተዋል፡፡

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ እና በክፍለ ከተማው ተቃቃመው ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ አቶ ዘመኑ ደሳለኝ በበኩላቸው በክፍለ ከተማው ፈተናውን ሰላማዊ በሆነ መልኩ ለማጠናቀቅ የጸጥታ አካላትን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻዎችን ያሳተፈ ስራ መሰራቱን ጠቁመው በዛሬው እለት በክፍለ ከተማው በሚገኙ የፈተና ጣቢያዎች ፈተናው ያለምንም እንከን መጀመሩን ሲገልጹ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ13 የፈተና ጣቢያ 3936 ተማሪዎች ፈተናውን እንደሚወስዱ የክፍለ ከተማው ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሪት ሙሉ በላቸው አስታውቀዋል፡፡

ዘንድሮ በአዲስ አበባ ፈተናው ከሰኔ 27 እስከ ሰኔ 29/2014 ዓ.ም ድረስ የሚሰጥ ሲሆን በሁሉም የፈተና ጣቢያዎች 1,800 ፈታኝ ፤450 ሱፐር ቫይዘር፤179 የፈተና ጣቢያ ኃላፊዎችን ጨምሮ በድምሩ 2,429 የፈተና አስፈጻሚዎች መመደባቸውን ከፈተና ዝግጅትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

0 Comments

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SITE VISITORS

  • 0
  • 0
  • 175
  • 2,114
  • 9,135
  • 234,185
  • 234,185