ቀን 25/9/ 2014 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ መምህራን እና የትምህርት አመራሮች በዛሬው እለት የሙያ ፈቃድ የጽሁፍ ምዘና ወሰዱ፡፡
የጽሁፍ ምዘናው በ9 የመመዘኛ ጣቢያዎች ለ9,241 መምህራን ርዕሰ መምህራን እና ሱፐር ቫይዘሮች የተሰጠ ሲሆን የጽሁፍ ምዘናውም ከ 80% የሚያዝ መሆኑን እና ቀሪው 20 % ደግሞ የማህደረ ተግባር ምዘና ተካሂዶ እንደሚያዝ ለማወቅ ችለናል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ የምዘና ሂደቱን ለመመልከት በዳግማዊ ሚኒሊክ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በሚገኘው የፈተና ጣቢያ ተገኝተው በሰጡት አስተያየት የመምህርነት ሙያ በትውልድም ሆነ በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ትልቁን አሻራ በማሳረፍ ላይ የሚገኝ ሙያ እንደመሆኑ የሙያ ብቃት ምዘናው የመምህሩንም እና የትምህርት አመራሩን በራስ መተማመን ከማሳደጉ ባሻገር ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችል ስርአት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊው አቶ ሳምሶን መለሰ በበኩላቸው ምዘናው መምህራኑ ያሉበትን የብቃት ደረጃ ለማረጋገጥና በሀገርም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችል ስርአት መሆኑን ጠቁመው የምዘና ሂደቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ በተመዛኝ ቁጥር እያደገ መምጣቱ መምህራኑም ሆኑ የትምህርት አመራሮቹ ለምዘና ስርአቱ ያላቸውን ፈቃደኛነት እንደሚያሳይ አስገንዝበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ምክትል ስራ አስካሄጅ ወይዘሮ ስንታየሁ ማሞ የሙያ ብቃት ምዘናው በ2004 ዓ.ም ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን 14,000 የሚሆኑ መምህራንና የትምህርት አመራሮች መመዘናቸውን እና የዘንድሮውን ምዘና በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን ቀደም ብሎ መረጃ የማሰባሰብና የህትመት ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸው ተመዝነው ብቁ የሆኑ መምህራንና የትምህርት አመራሮች በመዛኝነት መሳተፋቸውንም አስታውቀዋል፡፡
የአዲስ አበባ መምህራን ማህበር ፕሬዘዳንት አቶ ድንቅ አለም ቶሎሳ የሙያ ማህበሩ የምዘና ሂደቱ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው ተመዛኝ መምህራኑም በፍቃደኝነት ምዘናውን ለመውሰድ መምጣታቸው የሚደነቅ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡