(አዲስ አበባ 1/2/2016 ዓ.ም) በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ከቀለም ትምህርት ጎን ለጎን በተግባር እውቀትና ክህሎታቸውን የሚያሳድጉበት የሰርቶ ማሳያ ማዕከል እንዲሆኑ እየተሰራ ነው።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ትምህርት ቤቶች የሚገበዩትን የንድፈ-ኃሳብ እውቀት በተግባር እንዲደገፍ ትኩረት ተደርጓል።
ተማሪዎች አካባቢያቸውን በተለይም የሚመገቡትን አዝዕርትና ፍራፍሬ አውቀው ትምህርት ቤት ውስጥ እየተንከባከቡ እንዲያሳድጉ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በእርሻ ትምህርት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በዕውቀትና ክህሎት እንዲበቁና የዘርፉን እድገት እንዲያስቀጥሉ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል። ተግባር ተኮር የእርሻ ትምህርትን ትምህርት ቤቶች በሙሉ አቅጣጫ ወስደው ተግባራዊ እያደረጉ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በመዲናዋ የሚገኙ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች በከተማ ግብርና ውጤታማ ሆነው ለውጭ ማኅበረሰብ ማቅረብ መጀመራቸውን አመልክተዋል።
ተማሪዎችም ትምህርት ቤት ውስጥ ያለውን ተሞክሮና ልምድ ወደ ቤታቸውና አካባቢያቸው እንዲወስዱት የማድረግ ሥራ ልዩ ትኩረት መሰጠቱንም ተናግረዋል።
ከዚያም ባለፈ የከተማ ግብርና ልማት ለትምህርት ቤት ምገባ ግብዓት ማቅረብ በሚችል አግባብ እንዲሰናሰልና የአካባቢው ማኅበረሰብም በትምህርት ቤቱ የጓሮ አትክልቶችን እንዲያለማ አሠራር መዘርጋቱን ጠቅሰዋል።
ጎን ለጎንም በከተማ ግብርና ውጤታማ የሆኑ ትምህርት ቤቶችን ተሞክሮ ለማስፋት የሚያስችሉ የእርስ በርስ መማማሪያ መድረኮች መዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል።
በደጃዝማች ወንድይራድ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በከተማ ግብርና የጓሮ አትክልቶችን እየለማና ከብት እየደለበ የሚገኝ ሲሆን የትምህርት ቤቱ ርዕሰ-መምህር ካሱ ቱምሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በትምህርት ቤቱ እየተካሄደ ያለው የከተማ ግብርና በአዲሱ ሥርዓተ-ትምህርት በንድፈ-ኃሳብ የተማሩትን የእርሻ ትምህርት በተግባር እየተማሩ ነው ብለዋል።
ተማሪዎቹ በውጤታቸው የተሻሉ ዜጎች እንዲሆኑ በንድፈ-ኃሳብ ከሚማሩት የእርሻ ትምህርት በተጨማሪ በትምህርት ቤቱ በሚካሄደው የከተማ ግብርና ማሳያዎች በተግባር እንደሚማሩም ገልፀዋል።
ትምህርት ቤቱ የጓሮ አትክልቶችን በቅጥር ግቢው በሰባት ቦታዎች ከማልማት በተጨማሪ የከብት ማደለብ ሥራ በሰባት በሬዎች መጀመራቸውን ገልፀዋል።
ከጓሮ አትክልቶች የአካባቢውንና የትምህርት ቤቱን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑንም ርዕሰ-መምህሩ አቶ ካሱ ተናግረዋል።
0 Comments