(ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የሴቶች ወጣቶችና ህጻናት ማህበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ አባላት የተቋሙን የአንደኛ ሩብ አመት እቅድ አፈጻጸም የቢሮው የአጠቃላይ ካውንስል አባላት በተገኙበት ገምግሟል።
ቢሮው በዝግጅት ምዕራፍ አገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን እና የ2017 ዓ.ም ዕቅድ አዘጋጅቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ በማድረግ ወደተግባር መግባቱን በመገምገም በቀጣይ የተሻለ ስራ መስራት ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ ታስቦ የዛሬውን መርሀግብር ማዘጋጀት ማስፈለጉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የሴቶች ወጣቶችና ህጻናት ማህበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ዘይነባ ሽኩር አመላክተዋል።
በዝግጅት ምዕራፍ ከተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት መካከል የ2016 ዓ.ም አፈጻጸምን በመገምገም እና የ2017 ዓ.ም እቅድ በማዘጋጀት ወደ ተግባር መገባቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ለቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ገለጻ ባደረጉበት ወቅት አስረድተዋል።
ዶክተር ዘላለም አያይዘውም በኢ-ስኩል ሲስተም አማካይነት በሁሉም የመንግስት ትምህርት ቤቶች የ2017ዓ.ም የተማሪ ቅበላ ኦን ላይን በማካሄድ ወደ መማር ማስተማር ስራ መገባቱን ገልጸው ቢሮው በያዝነው የትምህርት አመት የተማሪዎችን የሒሳብና እንግሊዘኛ ውጤት ለማላቅ ስትራቴጂ ነድፎ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ በመግለጽ የተማሪዎች የምገባ አገልግሎትም ሆነ ዩኒፎርምን ጨምሮ ሌሎች የመማሪያ ቁሳቁሶች ከመሰራጨታቸው ባሻገር በኮሪደር ልማት ምክንያት የመኖሪያ አከባቢ ለቀየሩ ነዋሪዎች በሄዱበት አከባቢ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
በመርሀ ግብሩ በኢ-ስኩል ሲስተም የተካተቱ ስድስት ሞጁሎች ዝርዝር በቢሮው የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ልማትና ማስፋፋት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሆኑት በአቶ ደረጀ ዳኜ የቀረበ ሲሆን የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ በቀረቡት የአንደኛ ሩብ አመት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርቶች ላይ የተለያዩ አስተያየቶችን እና ጥያቄዎችን አቅርበው ምላሽ ተሰቷል።
የቋሚ ኮሚቴ አባላትም በቢሮ የተቋቋመውን የህጻናት ማቆያና ጂም ጎብኝተዋል፡፡
በትምህርት ሴክተሩ በዝግጅት ምዕራፍ በርካታ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የሴቶች ወጣቶችና ህጻናት ማህበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ አባላት አስታወቁ።
0 Comments