(ጥቅምት 29/2017 ዓ.ም) በውይይቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የአጠቃላይ ካውንስል አባላት የተሳተፉ ሲሆን የቢሮው የሪፎርምና አገልግሎት አሰጣጥ ክትትል ድጋፍና ምዘና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተስፋገኘሁ ለገሰ የስራ ክፍሎች የአንደኛ ሩብ አመት የክትትልና ድጋፍ ሪፖርት አቅርበው ውይይት ተካሂዷል።
ክትትልና ድጋፉ ሰባት የትኩረት መስኮችን እና አርባ የሚሆኑ ዝርዝር ተግባራትን መሰረት አድርጎ ስራ ክፍሎቹ ከአገልግሎት አሰጣጥና ሪፎርም ስራዎች ጋር በተገናኘ በአንደኛ ሩብ አመት የተከናወኑ ተግባራት ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ታስቦ መካሄዱን የሪፎርምና አገልግሎት አሰጣጥ ክትትል ድጋፍና ምዘና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተስፋገኘሁ ለገሰ አስታውቀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የቢሮ ኃላፊ አማካሪ ወይዘሮ አበበች ነጋሽ በክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤቶች በተካሄደ የአንደኛ ሩብ አመት የክትትልና ድጋፍ ግብረ መልስ ዙሪያ ከጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ጋር ተመሳሳይ ውይይት መካሄዱን ገልጸው በቢሮ የሚገኙ ስራ ክፍሎች በዝግጅት ምዕራፍ ከእቅድ ዝግጅት ጀምሮ የተሰጣቸውን ተልዕኮ ምን ያህል ውጤታማ እንዳደረጉ በማየት በቀጣይ የተሻለ ስራ መስራት እንዲቻል ታስቦ የተካሄደ ድጋፍና ክትትል መሆኑን አመላክተዋል።
ሁሉም ስራ ክፍሎች በድጋፍና ክትትል ሂደቱ የተሰጣቸውን ግብረ መልስ መሰረት በማድረግ እና ወደ ተቀራረበ ደረጃ በመምጣት በቀጣይ በግማሽ አመት በሚደረግ ምዘና ተቋሙ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግብ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚገባቸው ምክትል ቢሮ ኃላፊው አቶ ወንድሙ ኡመር አስገንዝበዋል።
በቢሮው ባሉ ዳይሬክቶሬቶች በተካሄደ የአንደኛ ሩብ አመት የክትትልና ድጋፍ ግብረ መልስ ዙሪያ ውይይት ተካሄደ።
0 Comments