በመስቀል ደመራ እና ኢሬቻ በአላት አከባበር ዙሪያ አጠቃላይ ሰራተኞች በተገኙበት ውይይት ተካሄደ።

by | ዜና

(መስከረም 9/2017 ዓ.ም) ውይይቱ የአብሮነት ፣ የወንድማማችነት/የእህታማማቾች የፍቅር መገለጫ የሆኑ በዓላቶችን በጋራ እናክብር! በሚል መሪ ቃል የተካሄደ ሲሆን በመርሀ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አበበ ቸርነት የ2017 ዓ.ም የመስቀል ደመራ እና ኢሬቻ በአላት አከባበርን በተመለከተ የተዘጋጀ ሰነድ አቅርበው ውይይት ተካሂዷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሲሳይ እንዳለ በውይይቱ መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት በሀገራችን ኢትዮጵያ የሚገኙ ሀይማኖታዊም ሆኑ ሕዝባዊ በአላቶች ትውፊታቸው ተጠብቆ ሀገራችንን በአለም አደባባይ ማስጠራት እንዲችሉ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ጠቁመው ዘንድሮ የሚከበሩትን የመስቀል ደመራ እና ኢሬቻ በአላት የብልጽግና ተምሳሌት በሆነችው አዲስ አበባ ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲከበር የቢሮው ሰራተኞች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ሁለቱም በአላት በርካታ ቁጥር ያለው የህብረተሰብ ክፍል አደባባይ ወጥቶ የሚያከብራቸው እንደመሆኑ በአላቱ አከባበር ለአብሮነታችን እና ለሀገር ግንባታ ባለው አስተዋጽኦ ልክ ሊከበር እንደሚገባ የቢሮ ኃላፊ አማካሪ ወይዘሮ አበበች ነጋሽ አስታውቀዋል።

የመስቀል ደመራ በአል ሀይማኖታዊ ትውፊቱ ተጠብቆ በደማቅ ስነስርአት ሲከበር መቆየቱን እንዲሁም ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ መገለጫና የገዳ ስርአት አካል የሆነ በአል መሆኑን በውይይቱ የተገለጸ ሲሆን የቢሮው ሰራተኞች በዓላቱ ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ እንዲከበሩ ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባቸው ተጠቁሟል።

0 Comments