ቀን 18/07/2014 ዓ.ም

በልደታ ክ/ከተማ ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ በህዝብና በመንግስት የተገነቡ 82 ፕሮጀክቶች ተመረቁ።

በዛሬው እለት በልደታ ክ/ከተማ በህዝብና በመንግስት የጋራ ጥረት ሲገነቡ የቆዩ ከ162 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው 82 ፕሮጀክቶች ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በተገኙበት ተመርቀዋል፡፡

በፕሮጀክቶቹ ምርቃት ስነስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት ለህዝብ ትንሽ የሚባል ፕሮጀክቶች የሉም ያሉ ሲሆን በተለይም የትውልድ መገንቢያ የሆኑ ትምህርት ቤቶች ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ናቸው ብለዋል፡፡

እነዚህ ፕሮጀክቶች በህዝብ ምክር ቤቶች አጀንዳ ሆነው ይቀርቡ እንደነበር ያስታወሱት ክብርት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች የተናገርነውን ቃላችንን መጠበቅ በመቻላችን ደስ ብሎናል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

እንደ ከንቲባ አዳነች ፕሮጀክቶቹ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ያሳካነው ፕሮጀክት ነው ያሉ ሲሆን ይህም ምንም ውዥንብር ቢኖር ፤ምንም አይነት ተግዳሮትና ፈተና ቢኖር ሊያስቆመን እንደማይችል ማሳያ ነው ዋናው ነገር መስራት ፤ መደማመጥ መተማመን ነው የሚጠበቅብን ብለዋል፡፡

የልደታ ክ/ከተማ ዋና ሰራ አስፈፃሚ አቶ አሰግደው ሃ/ጊዮርጊስ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት እነዚህን ፕሮጀክቶች ሙሉ ለመሉ በማጠናቀቅ ለምርቃት አብቅተናቸዋል ያሉ ሲሆን ይህ እውን እንዲሆን የአመራርሩ ፤ የባለሙያዎችና የህዝብ ጥረት የጋራ ውጤት ነው በማለት ገልፀዋል፡፡