በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተዘረጉ የስኩል ኔት መሰረተ ልማቶችን በአዲስ መልክ ስራ ለማስጀመር የሚያስችል ፕሮጀክት በዛሬው እለት ይፋ ሆነ።

by | ዜና

(ጥቅምት 27/2016 ዓ.ም)   የስኩል ኔት መሰረተ ልማት የዛሬ 10 አመት አከባቢ በወቅቱ በነበሩ 74 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በቴክኖሎጂ የተደገፈ ትምህርት እንዲያገኙ ታስቦ የተዘረጋ ሲሆን መሰረተ ልማቱ ወቅቱ የሚፈልገውን ቴክኖሎጂ አካቶ አገልግሎት መስጠት እንዲችልና በብልሽት ምክንያት አገልግሎት የማይሰጡት ዳግም ስራ እንዲጀምሩ ዘ ኒው ዌቭ ሀይቴክ ሶሉሽን የተሰኘ ሀገር በቀል ድርጅት ጨረታ አሸንፎ ወደ ስራ የሚገባበት የማስጀመሪያ መርሀ ግብር የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ እና የአዲስ አበባ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ አመራሮችን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ይፋ ሆኗል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ምህረቱ ደሳለኝ በመርሀ ግብሩ መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት የትምህርት ተቋማት የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ የሚችሉት ወቅቱን የጠበቀና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የትምህርት  መስጠት ሲችሉ በመሆኑ ቀደም ሲል በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተዘረጉ የስኩል ኔት መሰረተ ልማቶች ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ታስቦ ፕሮጀክቱ መጀመሩን ገልጸው ፕሮግራሙ ከትምህርት ቢሮ እስከ ትምህርት ቤት ድረስ ያሉ ዳታ ሴንተሮችን ማዘመንን ጨምሮ አዲስ ህንጻ በገነቡ ተቋማት ኔትወርክ መዘርጋትና ለዘርፉ ባለሙያዎች ስልጠና መስጠትን እንደሚያካትት አስታውቀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ወንድሙ ኡመር በበኩላቸው የስኩል ኔት መሰረተ ልማት ከአንድ ማዕከል የትምህርት ቤቶችን እንቅስቃሴ መከታተል ከማስቻሉ ባሻገር ቢሮው ቢሮው በቅርቡ ተግባራዊ የሚያደርገው የኢ-ስኩል ፕሮጀክት ውጤታማ እንዲሆን የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው ፕሮጀክቱ በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆን ኃላፊነቱን የወሰደው ድርጅት በአግባቡ አጠናቆ ማስረከብ እንደሚገባው ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል የትምህርት ጥራትን የሚያረጋግጥ እንደመሆኑ ድርጅቱ በ74ቱ ትምህርት ቤቶች በሚከፍታቸው 148 የአይ ሲቲ ላብራቶሪዎች 2,960 ዴስክቶፕ ኮምፒውተሮችን በማስገባት ተማሪዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማስቻሉ ባሻገር በትምህርት ቤቶቹ የደህንነት ካሜራዎች እንደሚገጠሙ የዘ ኒው ዌቭ ሀይ ቴክ ሶሉሽን ድርጅት ዋና ስራአስኪያጅ አቶ ሳሙኤል ሀብተወልድ ገልጸው ስራውም አልትራ ግሎባል ትሬዲንግ ከተሰኘ ድርጅት ጋር በአጋርነት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

 

0 Comments

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SITE VISITORS

  • 0
  • 0
  • 205
  • 6,046
  • 31,180
  • 147,475
  • 147,475