ሁለንተናዊ ርብርብ ለትምህርት ተቋማት ደረጃ መሻሻል በሚል መሪ ቃል በመካሄድ ላይ የሚገኘው 30ኛው ከተማ አቀፍ የትምህርት ጉባኤ በተለያዩ መርሀ ግብሮች ሲካሄድ ውሏል።

by | ዜና

አዲስ አበባ ነሀሴ 18 /2015 ዓ.ም ጉባኤው ከምሳ በኋላ በነበረው ቆይታ የቢሮው የእቅድ ዝግጅት ግምገማና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጌታሁን ለማ ባቀረቡት የ2015ዓ.ም እቅድ አፈጻጸም ሪፖርትና በ2016ዓ.ም እቅድ ፣ በፈተና ዝግጅትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዲናኦል ጫላ በቀረበው የተማሪዎች ውጤት ትንተና ሪፖርት  እንዲሁም  በምክትል ቢሮ ኃላፊው አቶ ወንድሙ ኡመር በቀረበው የልዩ ፍላጎትና ጎልማሶች ትምህርት ንቅናቄ ሰነድ ዙሪያ የተለያዩ አስተያየቶችን እና ጥያቄዎችን አቅርበው በቢሮው ኃላፊዎች ምላሽ ተሰቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ የጉባኤው ተሳታፊዎች ላነሱት ጥያቄዎችና በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ በሰጡት አስተያየት ከጉባኤው ተሳታፊዎች ለትምህርት ጥራት መረጋገጥም ሆነ ለተማሪዎች ውጤትና ስነምግባር መሻሻል የሚያግዙ ሀሳቦች መነሳታቸውን ገልጸው የትምህርት ስራው የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ የሚችለው አመራሩ ኃላፊነቱን በአግባቡ ሲወጣና መምህራን ቁርጠኛ ሆነው ሙያዊ ግዴታቸውን ሲወጡ እንደመሆኑ ቢሮው ለዚሁ ጉዳይ ትኩረት ሰቶ እንደሚንቀሳቀስ አስገንዝበዋል።

ዶክተር ዘላለም አክለውም በቀጣይ የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያስመዘግብና ትምህርት ቤቶች ለተለያዩ አዋኪ ተግባራት ተጋላጭ እንዳይሆኑ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመው በ2016ዓ.ም አዲሱ ስርአተ ትምህርት በሁሉም የመንግስትና የግል ትምህርት ተቋማት ወጥ በሆነ መልኩ ተግባራዊ ስለሚደረግ በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት መዋቅሮች አተገባበሩን በትኩረት መከታተል እንደሚገባቸው በመጥቀስ ዘንድሮ 3ኛ ክፍል ላይ ተግባራዊ የሆነው የብዝሀ ቋንቋ ትምህርት በቀጣዩ የትምህርት አመት ከ3ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ተግባራዊ እንደሚደረግና ለዚህም ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ አስታውቀዋል።

ጉባኤው በነገው እለት በ2015ዓ.ም የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎችና አፈጻጸማቸው የተሻለ ለሆኑ የትምህርት ተቋማት እውቅና በመስጠት እንደሚጠናቀቅ የወጣው መርሀግብር ያመለክታል።

0 Comments

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SITE VISITORS

  • 1
  • 184
  • 249
  • 2,420
  • 8,972
  • 243,954
  • 243,954