አዲስ አበባ ነሀሴ 19 /2015 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በጉባኤው መዝጊያ ለመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች ባስተላለፉት መልእክት የእውቅና ስነ-ስርዓቱ በተማሪዎች መካከል ጤናማ ፉክክር የሚፈጥር የሽልማት ስነ-ስርዓት መሆኑን ገልፀው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ የነገ የኢትዮጵያ ተስፋ ለሆኑ ተማሪዎች ምስጋና አቅርበዋል ።
በ2016 የትምህርት ዘመንም የተማሪን ስነ-ምግባርና ውጤት በማሻሻል የሚፈለገው ደረጃ ላይ ለማድረስና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሙሉ ጊዜያችሁን በመስጠት ለትምህርት ሥራ ስኬታማነት በጋራና በቅንጅት መስራት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ይጠበቃል ሲሉ አሳስበዋል :: ዶክተር ዘላለም አያይዘውም በ31ኛው የትምህርት ጉባኤ ከዚህ የተሻለ የአሰራር ስርዓትና ውጤት የምናስመዘግብበት እንደሚሆን እምነት አለኝ ብለዋል ::
በእለቱም የበጀት ዓመቱን ትምህርት ሥራ ስኬታማ ለማድረግ በተደረጉ እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላደረጉ ማለትም አዲሱን ስርአተ ትምህርት በሬድዮ እንዲቀረፅ ላደረጉ የተቋሙ ሰራተኞች ፣ በዘንድሮ የ6ኛና 8ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶችና ተማሪዎች ፣ ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ማየትና መስማት ለተሳናቸው ተማሪዎችና ትምህርት ፅህፈት ቤቶች እንዲሁም በሥራ አፈፃፀም ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አላማ ፈፃሚና ደጋፊ ዳይሬክቶሬቶች የእውቅናና ማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቷል ::
0 Comments